← All news
News Oct 19, 2026 · 19d ago

በኢትዮጵያ ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ለተሳሳተ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሰለባ መሆናቸው ተገለጸ

​በኢትዮጵያ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች እና ሀሰተኛ መረጃዎች አንጻር ከሴቶች ይልቅ ወንዶች በበለጠ ሁኔታ ለችግሩ ሰለባ መሆናቸውን የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ያካሄደው አዲስ ጥናት ይፋ አደርጓል። ​በጥናቱ ሂደት ላይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ክፍል የተሳተፉት ዶክተር አብዱልአዚዝ ዲኖ ለብስራት ሬዲዮ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ የጾታ ስብጥር ልዩነት ይስተዋላል ። ​በጥናቱ ግኝት መሰረት በኢትዮጵያ ከሚገኙ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መካከል 32 በመቶ ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 67 በመቶዎቹ ደግሞ ወንዶች ናቸዉ ። እንደ ዶክተር አብዱልአዚዝ ገለፃ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚስተዋሉ የሀሰት መረጃዎች ፣ የጥላቻ ንግግሮች እና ቴክኖሎጂን አላግባብ መጠቀም ስጋት እየሆኑ መጥተዋል ። በማህበራዊ ሚዲያዉ ላይ በሚለቀቁ የሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ሴቶች ተሳትፎ ቢኖራቸዉም በይበልጥ ወንዶች ተጋላጭ እየሆኑ መምጣታቸዉን ጥናቱ አመላክቷል ። ​ጥናቱ በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምና የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽእኖ በጥልቀት ለመረዳት ያለመ ሲሆን በዲጂታል ምህዳሩ ላይ የሚታዩ የጥላቻ ንግግሮችንና ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመቀነስ የታሰቡ የፖሊሲ ማሻሻያዎችና የመፍትሔ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባም ጠቁሟል።