በትግራይ በወታደራዊ ፍተሻና በሕዝብ ጥቆማ የተደበቁ የህወሓት ቡድን ወታደራዊ ትጥቆች በቁጥጥር ሥር ውለዋል
በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ተደብቀው የነበሩ ተተኳሾችና ሌሎች ወታደራዊ ትጥቆችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአዲስ ሪፖርተር የዜና ምንጮች አስታውቀዋል። በቀጠናው የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት በሚያካሂደው የተጠናከረ ፍተሻና ከሕብረተሰቡ በሚደርሱ ጥቆማዎች የተለያዩ ወታደራዊ ቁሳቁሶች እየተያዙ ነው። በደረሰን መረጃ መሠረት፣ በትላንትናው ዕለት በማዕከላዊ ትግራይ ዞን በዕዳጋ ዕሮብ አካባቢ በተደረገ ክትትል የቻይና ስሪት HYTERA ወታደራዊ መገናኛ ሬዲዮዎች 31 እና 122 የሬዲዮ ባትሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። በምሥራቃዊ ትግራይ ዞን በነበለት ወረዳም በሠራዊቱ ክትትልና በሕዝብ ጥቆማ የተለያዩ የመሣሪያ ተተኳሾች መያዛቸው ተገልጿል። ከተያዙት ውስጥ HE 37-55 ተብለው የተጠቀሱ ፀረ-ራዳርና ፀረ-ታንክ ሚሳይል ጥይቶች 45፣ የRPG ጥይቶች 8 እና የ76 ሚሊ ሜትር መድፍ ተተኳሾች 44 ይገኙበታል። ህወሓት ለልማት ሊውል የሚችልን ሀብት ለጦር መሣሪያ ግዢ በማዋል በተለያዩ ቦታዎች ትጥቅ አከማችቶበታል። የተያዙት ወታደራዊ ቁሳቁሶችም የቡድኑን የጦርነት ዝግጅት የሚያመለክቱ እና የህዝብን ሀብት ለግጭት ተልዕኮው መጠቀሙን የሚያሳይ ነው። በሌላ በኩል፣ የትግራይ ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊቱ መረጃ የመስጠት ሀላፊነታቸው እየተወጡ ነው። ይህም በክልሉ የጸጥታ ሁኔታን ለማሻሻልና የተደበቁ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ለማግኘት የሕዝብ ተሳትፎ እየተጠናከረ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ተገልጿል።