← All news
News Oct 19, 2026 · 20d ago

በህክምና ታሪክ የመጀመሪያው የመነጋገሪያ ክስተት፦ በአይን ምህዋር ውስጥ የበቀለው ያልተጠበቀ ጥርስ

በህክምናው ዓለም እጅግ ያልተለመደ እና አጃኢብ የሚያስብል አጋጣሚ በህንድ አራቪንድ የአይን ህክምና ሆስፒታል የተመዘገበ ሲሆን፣ የ16 ዓመት ታዳጊ በአይኑ አካባቢ ባጋጠመው እብጠት ምክንያት ወደ ህክምና ተቋም ካመራ በኋላ በምርመራ የተገኘው ውጤት መላውን የህክምና ባለሙያዎች አስገርሟል። ታዳጊው በግራ አይኑ የዐይን ሽፋሽፍት አካባቢ ምንም አይነት ህመም የሌለው እብጠት ተስተውሎበት ወደ ሆስፒታል ያመራ ሲሆን፣ ከአንድ ወር ገደማ በኋላ በዐይን ሽፋሽፍቱ እና በቅንድቡ መካከል ሁለት አነስተኛ፣ ጠንካራ እና ነጭ የሆኑ አካላት ብቅ ብለዋል። ጉዳዩ ያሰጋቸው የህክምና ባለሙያዎች የተከሰተው ነገር ጥርስ ይሁን ወይም አልፎ አልፎ የሚከሰት እጢ ለመለየት የሲቲ ስካን ምርመራ አድርገዋል። በምርመራው ውጤትም በቆዳው ስር የታዩት ሁለት ነጫጭ ጫፎች በግራ አይኑ የላይኛው ምህዋር ውስጥ ሙሉ በሙሉ አድጎ ከተገኘ አንድ ጥርስ የተገኙ መሆናቸው ተረጋግጧል። የጥርስ ስርም የአይኑን ምህዋር ከከበበው አጥንት ጋር ተጣብቆ ተገኝቷል። ሐኪሞች ባደረጉት ስኬታማ ቀዶ ህክምና ጥርሱን ከአይኑ ምህዋር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ያወጡት ሲሆን፣ ከተወገደ በኋላ በተደረገ ምርመራ ጥርሱ ከምንም አይነት እጢ ጋር የተያያዘ አለመሆኑ ተረጋግጧል። ይህ ህክምናዊ ክስተት ኤክቶፒክ ቱዝ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህም ጥርስ ከአፍ ውጭ ባሉ የሰውነት ክፍሎች ላይ የሚበቅልበት እጅግ አልፎ አልፎ የሚከሰት ሁኔታ ነው። በጥናት እና በህክምና ታሪክ ጥርስ በአይን ምህዋር የላይኛው ክፍል ሲበቅል የመጀመሪያው ተመዝጋቢ አጋጣሚ በመሆኑ በዘርፉ ትልቅ ትኩረት ስቧል።