የ“No More ስጋ” ዘመቻ በአዲስ አበባ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ትልቅ መነጋገሪያ እየሆነ ይገኛል።
በአዲስ አበባ ከተማ እየታየ ያለውን ከልክ ያለፈ የስጋ ዋጋ ጭማሪ ለመቃወም በማህበራዊ ሚዲያዎች የተጀመረው “የስጋ ዋጋ ይቀንስ no more ስጋ” የተሰኘ የቦይኮት ንቅናቄ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ ይገኛል። ዘመቻው በቲክቶክ እና በፌስቡክ መድረኮች በስፋት እየተሰራጨ የሚገኝ ሲሆን፣ የዋና ከተማዋ ነዋሪዎች ከፍተኛ የሆነውን የዋጋ ጭማሪ በመቃወም ድምፃቸውን እያሰሙበት ይገኛሉ። ሸማቾች የስጋ ቤቶች የጣሉትን ተገቢ ያልሆነ ዋጋ እንዲያስተካክሉ ግፊት ለማድረግ፣ ጥያቄው እስኪመለስ ድረስ ስጋ አለመግዛትና ፍጆታን ማቆም እንደ አማራጭ እንዲወሰድ እየጠየቁ ይገኙበታል የከተማ አስተዳደሩ የገበያ መረጋጋት ለመፍጠር የተለያዩ እርምጃዎችን ቢወስድም፣ በተለይ በትልልቅ የሉካንዳ ቤቶች እና ሬስቶራንቶች የሚቀርበው የስጋ ዋጋ ማርገብ አልቻለም። በአንዳንድ ታዋቂ የከተማዋ ስጋ ቤቶች የአንድ ኪሎ ግራም ስጋ ዋጋ እስከ 6 ሺህ ብር መድረሱ መነገሩ የህብረተሰቡን ቁጣ አባብሶታል። ይህንን ተከትሎ የዘመቻው ተሳታፊዎች ህብረተሰቡ ፊቱን ወደ ጥራጥሬና አትክልት ምርቶች እንዲያዞር ጥሪ በማድረግ ላይ ናቸው። ይህ የዲጂታል አንድነት በስጋ አቅራቢዎችና ሻጮች ላይ የገበያ ግፊት በመፍጠር ዋጋው ተመጣጣኝ እንዲሆን ለማድረግ ያለመ ነው።