← All news
News Oct 18, 2026 · 20d ago

በአዲስ አበባ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሦስት ሰዎች ህይወት አለፈ

የመጀመሪያው አደጋ የደረሰው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 13 ልዩ ቦታው ጀሞ ቅዱስ ሚካኤል መብራት ከቀኑ 9፡30 አካባቢ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የትራፊክ አደጋ ምርመራ መምሪያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር መንግስቱ ታደሰ እንደገለፁት የጉዞ አቅጣጫውን ከአየር ጤና ወደ ጀርመን አደባባይ ያደረገው ሲኖትራክ ተሽከርካሪ መብራት ይዟቸው ቆመው የነበሩ 10 ተሽከርካሪዎችን እና አንድ የመብራት ፖል ላይ በመግጨት የንብረት ጉዳት አድርሷል ብለዋል፡፡ በአደጋው በትራንስፖርት ተሽከርካሪ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩ የ44 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አንዲት እናት ላይ የሞት፣ በአንድ ሌላ ትራንስፖርት ተጠቃሚ ላይ ከባድ የአካል ጉዳት እንዲሁም በ11 ሰዎች ላይ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ያስታወሱት ኃላፊው የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በዚያው ዕለት ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ላይ ደግሞ በክ/ከተማው ወረዳ 01 ጀሞ ሦስት አካባቢ ፒክአፕ ተሽከርካሪ ይዞ ከጀሞ ቅዱስ ሚካኤል ወደ ጀሞ ሶስት ሲጓዝ የነበረው አሽከርካሪ ከቀኝ ወደ ግራ ሲሻገር በነበረ ግለሰብ ላይ የሞት አደጋ ያደረሰ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል። በዕለቱ ከምሽቱ 4፡30 አካባቢ ደግሞ በዚያው ክ/ከተማ ወረዳ 15 ሀጫሉ መንገድ አካባቢ ሀዩንዳይ ተሽከርካሪን በመያዝ ወደ ጋርመንት እያሽከረከረ የነበረ ግለሰብ ከመንገድ ጠርዝ ጋር በመጋጨት የአሽከርካሪው ህይወት ማለፉን አብራርተዋል፡፡ በአንድ ቀን ብቻ በደረሱ አደጋዎች የሦስት ሰዎች ህይወት አልፏል ።