ሚኒስቴሩ አስቸኳይ የጥንቃቄ መልዕክት አስተላለፈ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ስም ከሚፈጸም ማጭበርበር ዜጎች እንዲጠነቀቁ አስቸኳይ የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ ሚኒስቴሩ፣ አጭበርባሪዎቹ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን ስም፣ አርማ፣ የከፍተኛ አመራሮችን ፎቶና ፊርማ በመጠቀም ሐሰተኛ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ማስታወቂያዎች በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገፆች እየተሰራጩ ይገኛሉ ብሏል። እነዚህ ማስታወቂያዎች በተለያዩ ሀገራት የሥራ ዕድል እንደሚያመቻቹ የሚገልፁ፣ ሂደቱን ለማስጨረስ ቀስ በቀስ ገንዘብ የሚጠይቁ እና ገንዘብ ከተቀበሉ በኋላ አድራሻቸውን የሚያጠፉ ስለመሆናቸዉም አስጠንቅቋል፡፡ ሚኒስቴሩ አክሎም በሚኒስቴር ምስሪያቤቱ በኩል ከተዘረጋው ሕጋዊ ስርዓት ውጪ ለየትኛውም አካል የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን በተመለከተ ውክልና የሰጣቸው ተቋማት አለመኖራቸዉን አመላክቷል፡፡ በመኾኑም ሕብረተሰቡ በእነዚህ አሳሳች ማስታወቂያዎች ተታልሎ ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት እንዳይዳረግ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።