ኢራን ሆርሙዝን ለመክፈት ያቀረበችውን የሰላም ጥሪ አሜሪካ እንድትቀበል አሳሰበች
ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥን በድጋሚ ለመክፈት ለአሜሪካ ያቀረበችው የሰባት ቀናት የድርድር ሀሳብ አሁንም በጠረጴዛ ላይ መኖሩን ገለጸች። የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ፣ ዋሺንግተን ቅን ፍላጎት ካሳየች የባህር መስመሩን በድጋሚ የመክፈት እድል እንዳለ አስታውቀዋል። አራቅቺ በባግዳድ ለኢራን መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ የቴህራን አቋም ግልጽ መሆኑንና ለአሜሪካ በቀረበው የሰባት ቀናት የድርድር ሀሳብ ላይ መመስረቱን ገልጸዋል። ኢራን ያቀረበችው ሀሳብ ከተቀበለች የሆርሙዝ ሰርጥ በስድስት ቀናት ውስጥ ሊከፈት እንደሚችልም ተናግረዋል። በኢራን የቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች በኢራን ወደቦች ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ፣ በነዳጅ ምርት ኤክስፖርት ላይ ያሉ ማዕቀቦች እንዲሻሩ እና በቀጠናው ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ የሚጠይቁ ናቸው። በተቃራኒው አሜሪካ የኢራን የኑክሌር ፕሮግራም የድርድሩ አካል መሆን እንዳለበት አቋም መያዟ ዋናው የልዩነት ነጥብ ሆኗል። የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄ.ዲ. ቫንስ በበኩላቸው፣ ኢራን የዩራኒየም ማበልጸግ አቅሟን በተጨባጭ መቀነስ እንዳለባት ገልጸዋል። ቴህራን ግን ቅድሚያው ለሆርሙዝ ሰርጥ ደህንነት መመለስና የዓለም አቀፍ የነዳጅ እና የጋዝ ንግድ መስመር እንደገና እንዲሰራ መደረግ እንደሆነ አቋሟን አስታውቃለች።