የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች
ሊያውቁት የሚገባ አስደንጋጭ ዜና * ከ200 ሚ. ብር በላይ የዘረፉት በቁጥጥር ሥር ዋሉ! በቴክኒክ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኛነት እና በልዩ ልዩ የማታለያ ዘዴዎች ከ658 በላይ ዜጎች ላይ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የኢኮኖሚ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ 37 ግለሰቦች በፌደራል ፖሊስ እና በጸጥታ አካላት ጥምር ኦፕሬሽን በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ተጠርጣሪዎቹ "ሽልማት ደርሶዎታል"፣ "ሞባይል ባንኪንግ ሲስተም ልናዘምንልዎት ነው" እንዲሁም "የባንክ ሂሳብዎን ከፋይዳ መታወቂያ ጋር እናስተሳስራለን" በማለት በውሸት ስም በመደወል የይለፍ ቃል (PIN) እና ሚስጥራዊ ቁጥሮችን (OTP) በመጠየቅ ሕገ-ወጥ ዝርፊያ ሲፈጽሙ እንደነበር በምርመራ ተረጋግጧል። ወንጀለኞቹ በተቀናጀ መልኩ መኖሪያ ቤቶችን በመከራየት፣ በተለያዩ ግለሰቦች ስም የተከፈቱ በርካታ የባንክ አካውንቶችን እና ሲም ካርዶችን በመጠቀም ወንጀሉን ሲፈጽሙ የቆዩ ሲሆን፤ በቁጥጥር ሥር በሚውሉበት ወቅትም ከ9 በላይ ተሽከርካሪዎች፣ 1 ሞተር ሳይክል፣ 114 ሞባይል ቀፎዎች እና 478 ሲም ካርዶች በዕቃ ማስረጃነት ተይዘውባቸዋል። ፖሊስ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች በዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPApp)፣ በነጻ የስልክ መስመር (991) ወይም በአካል በመቅረብ ጥቆማ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል። ባንኮች በምንም መልኩ በግል ስልክ በመደወል ሚስጥራዊ መረጃዎችን እንደማይጠይቁ ሕብረተሰቡ አውቆ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ፖሊስ አሳስቧል። ማንኛውም አጠራጣሪ የስልክ ጥሪ ሲያጋጥም ወዲያውኑ ለፖሊስ ወይም ለባንክ ማሳወቅ ህይወትንና ንብረትን ከከፍተኛ ማጭበርበር የሚታደግ በመሆኑ ህብረተሰቡ የንቁ ተሳትፎ ሚናውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።