በሌ/ጄነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ የሚመራው የትግራይ ሰላምና ለውጥ ምክር ቤት በነበረበት አደረጃጀት እንደማይቀጥል አስታወቀ
በሌተናል ጄነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ የሚመራው “የትግራይ ሰላም እና ለውጥ ምክር ቤት” ከአሁን በኋላ በተቋቋመበት አደረጃጀት እንደማይቀጥል አስታወቀ። ምክር ቤቱ በትግራይ ክልል የሽግግር ሂደቶችን ለማመቻቸት ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን፣ ፌደራል መንግሥት ቀጣይ የሽግግር ተግባራትን ራሱ ለመምራት መወሰኑ የምክር ቤቱ በነበረበት መዋቅር እንዳይቀጥል ምክንያት መሆኑን ገልጿል። ምክር ቤቱ በተጨማሪም በትግራይ የሚታየው “ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ድል” እንዲገኝ የበኩሉን ሚና መወጣቱን አመልክቷል። ምክር ቤቱ ግንቦት 2018 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን፣ ከህወሓት የተለዩ ወይም የተቃረኑ ፖለቲከኞችን፣ የትግራይ ፖለቲካ ፓርቲዎችን እና ከአስር በላይ የሲቪል ማኅበራትና የሚዲያ አካላትን አካትቶ እንደነበር ተገልጿል። ከምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች መካከል በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ፣ ወለዶ ትግራይ፣ አረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት እና ትንሳኤ ሰባ እንደርታ ይገኙበታል። ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ በተጨማሪም የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተደራዳሪ ግለሰቦች እና የሲቪል ማኅበራት አባላት በምክር ቤቱ ውስጥ ተሳትፈዋል። የምክር ቤቱ ውሳኔ ይፋ የሆነው፣ ፌደራል መንግሥት ለትግራይ ክልል ቀጣዮቹን ስድስት ወራት የሚመራ ባለአደራ አስተዳደር ማቋቋሙን ካስታወቀ ከሰዓታት በኋላ መሆኑም ተገልጿል። ይህም በትግራይ ቀጣይ የሽግግር ሂደት የሚኖረውን የአመራር መዋቅር አዲስ አቅጣጫ የሚይዝ መሆኑን ያመለክታል።