← All news
News Oct 17, 2026 · 22d ago

“በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከቤተ መንግሥት ሳንወጣ ቃል የተገባልንን ኮሪደር እንሠራለን፤ መቐለንም እናስውባለን” - የመቐለ ከተማ ከንቲባ

በትግራይ ባለአደራ አስተዳደር የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሆነው የተሾሙት ሽሻይ አማረ (ዶ/ር)፣ የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ማስጠበቅ፣ ሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ እና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ማሻሻል ቀዳሚ የሥራ አቅጣጫዎቻቸው መሆናቸውን ገለጹ። ከንቲባው ይህንን ያስታወቁት በይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰራጩት መልዕክት ነው። ከንቲባው እንደገለጹት፣ በመቐለ ከተማ የኮሪደር ልማት ለማከናወን ከፌዴራል መንግሥት ቃል ተገብቷል። ሽሻይ አማረ፣ “በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከቤተ መንግሥት ሳንወጣ ቃል የተገባልንን ኮሪደር እንሠራለን፤ መቐለንም እናስውባለን” በማለት የልማት ዕቅዱን ለማስፈጸም ቁርጠኛ አቋም መያዛቸውን አስታውቀዋል። በተጨማሪም በመላው ትግራይ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን እንደሚሠሩ ገልጸዋል። ከንቲባው በሽግግር ወቅት የመቐለን ሕዝብ የማገልገል ኃላፊነት ለእሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የከተማዋ ለውጥ ፈላጊዎች የተሰጠ አደራ መሆኑን አስገንዝበዋል። “አብረን አደራችንን እንደምንወጣ እምነቴ ነው” በማለትም የሕዝቡን ትብብር ጠይቀዋል። ሽሻይ አማረ (ዶ/ር) በትግራይ ጦርነት ወቅት ወደ በረሃ ከወረዱ የህወሓት አመራሮች መካከል አንዱ ሲሆኑ፣ ከጦርነቱ በኋላ ለአጭር ጊዜ የትግራይ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል። በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በህወሓት አመራሮች መካከል በተፈጠረው የፖለቲካ ክፍፍል፣ በጌታቸው ረዳ የሚመራውን የለውጥ ኃይል ከደገፉ አመራሮች መካከል የነበሩ እንዲሁም የትግራይ ስምረት ፓርቲን ከመሠረቱ አመራሮች መካከል አንዱ ናቸው።