ወላጅ እናቱን በተደጋጋሚ በማስፈራራትና ንብረቷን ያለፈቃዷ በመውሰድ የተጠረጠረው ግለሰብ በድሬዳዋ ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋለ።
ወላጅ እናቱን በተደጋጋሚ በማስፈራራትና ዛቻ ወንጀል በመፈጸም፣ እንዲሁም ንብረቶቿን ያለፈቃዷ በመውሰድና በመሸጥ ለግል ጥቅሙ ሲያውል ነበር በሚል የተጠረጠረው ማራናታ ቢተው የተባለ ግለሰብ በድሬዳዋ ፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ። ግለሰቡ ቀደም ሲልም ወላጅ እናቱን በማስፈራራትና ዛቻ ወንጀል በመፈጸም ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ ለፍርድ ቤት መቅረቡም ተገልጿል። በወቅቱ የግል ተበዳይ የሆኑት ወላጅ እናቱ ይቅርታ እንዲደረግለት ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ ግለሰቡ (15,000) አስራ አምስ ሺህ የብር ቅጣት እና በሁለት አመት ገደብ ከእስር መለቀቁን ፖሊስ ገልጿል። ይሁን እንጂ ግለሰቡ ከዚህ በፊት በተፈጸመው ድርጊት ሳይታረም እንደገና እናቱን በማስፈራራትና ንብረቶቿን በግዴታ በመውሰድ ለግል ጥቅሙ ሲያውል እንደነበር ተጠርጥሯል። የዚህ ድርጊት መፈጸሙን ተከትሎ እናቱ ጉዳዩን በግል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በማጋራት ለሕዝብ ይፋ ካደረጉ በኋላ፣ ጉዳዩ ለድሬዳዋ ፖሊስ መድረሱ ተገልጿል። ድሬዳዋ ፖሊስም በጉዳዩ ላይ ባደረገው ጥብቅ ክትትል ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል። በቤተሰብ ውስጥ መከበርና መጠበቅ ያለባት ወላጅ እናት ለተደጋጋሚ ማስፈራራትና ዛቻ መጋለጧ ተገቢ አለመሆኑ ድሬዳዋ ፖሊስም በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ ምርመራውን እያካሄደ ይገኛል ።