ደንበኞች የቆጣሪ ንባባቸውን በቴሌግራም ቻትቦት የሚያሳውቁበት አዲስ አሰራር ወደ ሥራ ገባ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የድህረ ክፍያ ተጠቃሚ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ወርሃዊ የቆጣሪ ንባባቸውን በራሳቸው ማሳወቅ እንዲችሉ የቴሌግራም ቻትቦት አበልጽጎ ወደ ሥራ አስገብቷል። አዲሱ አሰራር በመደበኛው የቆጣሪ ንባብ ወቅት ንባባቸው ያልተወሰደላቸው ደንበኞች ትክክለኛውን የቆጣሪ ንባብ በተፈቀደው የጊዜ ገደብ፣ ማለትም ከመደበኛው የንባብ ወቅት ማብቂያ በኋላ ባሉት አራት ተከታታይ ቀናት ውስጥ፣ በቀጥታ እንዲያስገቡ ያስችላል። አገልግሎቱ በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ ነጠላ ፌዝ ቆጣሪ ያላቸው የድህረ ክፍያ ተጠቃሚ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ብቻ የተዘጋጀ ነው። ደንበኞች በቴሌግራም ላይ @Eeuchatbot ብለው በመፈለግ ወይም በተቋሙ ይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ የቻትቦቱን ማስፈንጠሪያ በመጠቀም አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ። በአዲስ አበባ፣ በጅማ እና በአጋሮ ከተሞች መደበኛው የቆጣሪ ንባብ ወር በገባ ከ13ኛው እስከ 26ኛው ቀን ይካሄዳል። በዚህ ወቅት ቆጣሪያቸው ያልተነበበላቸው ደንበኞች ከ27ኛው እስከ 30ኛው ቀን ድረስ በቻትቦቱ አማካኝነት ንባባቸውን ማስገባት ይችላሉ። ከእነዚህ ከተሞች ውጭ ለሚገኙ ደንበኞች የማስገቢያ ጊዜው በየንባብ ቡድናቸው መሠረት እንደሚከተለው ይሆናል፦ 👉 ቡድን 1፦ ከወሩ 21ኛው እስከ 24ኛው ቀን 👉 ቡድን 2፦ ከወሩ 28ኛው ቀን እስከ ቀጣዩ ወር 1ኛው ቀን 👉 ቡድን 3፦ ከወሩ 5ኛው እስከ 8ኛው ቀን 👉 ቡድን 4፦ ከወሩ 12ኛው እስከ 15ኛው ቀን ደንበኞች የቆጣሪ ንባባቸውን ለማስገባት የሚከተሉትን ደረጃዎች መከተል ይችላሉ፦ ✅ በቴሌግራም ላይ @Eeuchatbot ብለው በመፈለግ ቻትቦቱን ያግኙ። ✅ ቻትቦቱን ካስጀመሩ በኋላ “Send Meter Reading” የሚለውን አማራጭ ይምረጡ። ✅ ባለ 12 ዲጂት የደንበኛ መለያ ቁጥርዎን (Contract Account Number) ያስገቡ። ✅ ትክክለኛውን የቆጣሪ ንባብ በማስገባት ይላኩ። ደንበኞች ንባባቸውን ማስገባት የሚችሉት በተፈቀደው የጊዜ ገደብ ውስጥ ብቻ ነው። ከተፈቀደው ጊዜ በፊት ወይም ከገደቡ በኋላ ንባብ እንዲሁም የተሳሳተ ንባብ ማስገባት አይቻልም። ስለሆነም ደንበኞች ትክክለኛውን የቆጣሪ ንባብ በተወሰነው ጊዜ ውስጥ ማስገባታቸው አስፈላጊ ነው። ይህ አዲስ አሰራር በቆጣሪ ንባብ አለመወሰድ ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ የፍጆታ ሂሳብ አዘገጃጀት ችግሮችንና የክፍያ መዘግየት ቅሬታዎችን ለመቀነስ የታለመ ሲሆን፣ ደንበኞች በቀላሉና በተመቻቸ መንገድ የቆጣሪ ንባባቸውን እንዲያሳውቁ ዕድል ይፈጥራል።