የሱዳኑ ጀኔራል አል-ቡርሃን ለትራምፕ ደብዳቤ ላኩ‼
የሱዳን ጦር አዛዥና የሀገሪቱ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጀነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደብዳቤ መላካቸውን አስታወቁ። ጀነራሉ በመልዕክታቸው የሱዳን መንግሥት በአሜሪካ የሚመሩትን የሰላም ጥረቶች እንደሚደግፍ በማረጋገጥ፣ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት፣ አንድነትና የግዛት ሙሉነት በሚያስጠብቅ መልኩ ከሁሉም ወገኖች ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህ የዲፕሎማሲ እርምጃ በሱዳን ጦርና በጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ በሚመራው የፈጣን ድጋፍ ኃይል (RSF) መካከል የሚካሄደው ጦርነት በቀጠለበት ወቅት መፈጸሙ ትኩረት ስቧል። በዚህ ሁኔታ የሱዳን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ላይ የተሰጠው አጽንዖት በማንኛውም የሰላም ድርድር የመንግሥትን ሚናና የሀገሪቱን የፖለቲካ ወደፊት አቅጣጫ ለመወሰን ያለውን አስፈላጊነት ያመለክታል። በሌላ በኩል፣ አል-ቡርሃን በቀጥታ ለትራምፕ መልዕክት መላካቸው የዋሽንግተንን ድጋፍ ለማግኘትና በሱዳን የሰላም ሂደት ላይ የመንግሥታቸውን አቋም ለማስጠንከር የተደረገ የዲፕሎማሲ ጥረት እንደሆነ ተገልጿል።