← All news
News Oct 16, 2026 · 23d ago

ዩኬ ኤርትራውያን ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ የቪዛ እገዳ እንደምትጥል ዛተች

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ኤርትራ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙና በትናንሽ ጀልባዎች ወደ ዩኬ ከገቡ በኋላ ወንጀል የፈጸሙ ወይም በአገሪቱ ለመቆየት ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎቿን መልሳ ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆነች፣ በኤርትራውያን ላይ የቪዛ እገዳ ሊጥል እንደሚችል አስጠነቀቀ። የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሻባና ማሕሙድ ኤርትራ ከሌሎች አገራት በተለየ ሁኔታ ዜጎቿን መልሳ ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልሆነች ገልጸዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሐሙስ ጀምሮ የኤርትራ ዲፕሎማቶች ከለንደን ውጭ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ገደብ እንደሚጣል ተነግሯል። በዚህም ዲፕሎማቶቹ የቅድሚያ ፈቃድ ሳያገኙ ከለንደን በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ እንዳይንቀሳቀሱ ይገደባሉ። በተጨማሪም ለከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚሰጠው ፈጣን የቪዛ አገልግሎት እንደሚቆም ተገልጿል። የዩኬ መንግሥት በትናንሽ ጀልባዎች ወደ አገሪቱ የሚገቡ ስደተኞችን የመቀበል ጉዳይ ላይ ከተለያዩ አገራት ጋር እየተወያየ ሲሆን፣ ዜጎቻቸውን መልሰው ለመቀበል ፈቃደኛ ባልሆኑ አገራት ላይ የቪዛ እገዳን ጨምሮ የተለያዩ ጫናዎችን ለመጠቀም እንደሚያስብ አስታውቋል። እስከ ሰኔ ባሉት 12 ወራት ውስጥ በትናንሽ ጀልባዎች ወደ ዩኬ ከገቡ ስደተኞች መካከል ኤርትራውያን 18 በመቶ ያህሉ ተይዘዋል። ሚኒስትሯም ኤርትራ በዚህ ጉዳይ ላይ ትብብር ካላደረገች እርምጃ እንደሚወሰድባት በመግለጽ፣ ትብብር በማያደርጉ ሌሎች አገራት ላይም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ እንደማይመለሱ አስጠንቅቀዋል።