← All news
News Oct 15, 2026 · 23d ago

የተሻሻለው የጉምሩክ አዋጅ ለነጋዴዎች በርካታ ማቃለያዎችን ይዞ መጥቷል ተባለ

የተሻሻለው የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 1425/2018 የንግዱን ማኅበረሰብ የሚጠቅሙና አሠራርን የሚያቃልሉ በርካታ ለውጦችን ማካተቱን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።   የኮሚሽኑ የሕግ ተገዢነት ዘርፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ ባሳ እንዳስታወቁት፤ አዲሱ አዋጅ ወደ አገር በሚገቡ ዕቃዎች ላይ የሚከፈለውን ቀረጥና ታክስ በአንድ ጊዜ መክፈል ለማይችሉ ነጋዴዎች፣ ዕቃዎቻቸውን በክፍልፋይ ማስለቀቅ የሚችሉበትን ዕድል ፈጥሯል።   ከዚህ ቀደም ነጋዴዎች በርካታ ኮንቴይነሮችን በአንድ ሰነድ ሲያስመጡ የሁሉንም ዕቃዎች ቀረጥ ሙሉ በሙሉ መክፈል ወይም ተመጣጣኝ ማስያዣ ማቅረብ ይገደዱ እንደነበር ይታወሳል ሲል ኮሚሽኑ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አሳውቋል።   በተጨማሪም ነጋዴዎች አስፈላጊውን የጉምሩክ ሥነ-ሥርዓት ለማጠናቀቅ የሚያስችላቸው የጊዜ ገደብ ተራዝሟል። በዚህም መሠረት በየብስ ለሚጓጓዙ ዕቃዎች ይሰጥ የነበረው የ15 ቀናት ገደብ ወደ 45 ቀናት፤ በአየር ለሚጓጓዙ ዕቃዎች ደግሞ የ10 ቀናት ገደብ ወደ 30 ቀናት ከፍ እንዲል ተደርጓል።   ኃላፊው አክለው እንደገለጹት፤ የተደረጉት ማሻሻያዎች ነጋዴዎች የጉምሩክ ሥነ-ሥርዓቶችን በበቂ ጊዜ አጠናቀው ዕቃዎቻቸውን በወቅቱ እንዲያወጡ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።