← All news
News Oct 14, 2026 · 24d ago

ኢትዮጵያ በአዲሱ የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካ

በዓመት እስከ 80 ቢ. ዶላር ገቢ ታገኛለች ተባለ በአዲስ አበባ ቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባና ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኑ የተነገረለት አዲሱ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ፣ ሙሉ አቅሙን ሲጠቀም በዓመት ከ600 ቶን በላይ ወርቅ የማጣራት አቅም እንዳለው ቢቢሲ ኒውስ ዴይ ዘግቧል። ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና ከዱባዩ ሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ ጋር በመተባበር የተገነባው የ50 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክቱ፤ የወርቅ ምርትን በአገር ውስጥ በማጣራት የተሻለ የገበያ ዋጋ ለማግኘትና ኢትዮጵያን የቀጣናው ማዕከል ለማድረግ ያስችላል ተብሏል። ከቢቢሲ ኒውስ ዴይ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ብሩክ ታዬ እንደገለጹት፤ ፋብሪካው መቶ በመቶ ሙሉ አቅሙን ሲጠቀም በወቅቱ የገበያ ዋጋ እስከ 80 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘት ይችላል። ቀደም ሲል ጥሬ ወርቅ ወደ ውጭ በመላኩ ምክንያት ከሚገኘው ገቢ ጎን ለጎን፣ አሁን ማጣሪያው መከፈቱ ከወርቅ ኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ ከእጥፍ በላይ ሊያሳድገው እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስረድተዋል። በዚህ አጋርነት ሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ 49 በመቶ ድርሻ ሲኖረው፣ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ደግሞ 51 በመቶ ድርሻ  እንዳለው ተገልጿል። ከወርቅ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ቀጥታ ወደ ብሔራዊ ባንክ በመግባት እንደ ነዳጅ፣ ማዳበሪያ እና መድኃኒት ያሉ አስፈላጊ የውጭ ግብዓቶችን ለመግዛት የሚያገለግል ሲሆን፤ ለአገር ውስጥ ባንኮችም የውጭ ምንዛሪ ጨረታዎች እንዲቀርቡ እያደረገ እንደሚገኝ ተነግሯል።