3,460 የክላሽንኮቭ ጥይቶች በቆቦ–ወልድያ መንገድ ተያዘ
በሰሜን ወሎ ዞን ከቆቦ ከተማ ተነስቶ ወደ ወልድያ ከተማ ሊገባ የነበረ 3,460 የክላሽንኮቭ ተተኳሽ ጥይት በጸጥታ አካላት ተያዘ። ጥይቶቹ በኮድ-3-14122 አአ ታርጋ ቁጥር ባጃጅ ላይ ከሌሎች ዕቃዎች ጋር ተደብቀው፣ መሸፈኛውም የእንስሳት መኖ በማድረግ ለማጓጓዝ መሞከሩን የወልድያ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አበራ ካሳው ገልጸዋል። ተሽከርካሪው ወልድያ ከተማ ሲገባ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በተሰጠ ጥቆማ መሠረት በራያ በር ዳቦ ቤት ኬላ ላይ በቁጥጥር ስር ውሏል። በተደረገው ፍተሻም ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ሊዘዋወሩ የነበሩት 3,460 ጥይቶች ተገኝተዋል። ኮማንደር አበራ ለጸጥታ አካላት የሚደረገው የህብረተሰቡ ትብብር የሕግ ማስከበር ሥራውን እያጠናከረ መሆኑን ገልጸው፣ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ እና ተተኳሽ ጥይቶችን ለመከላከል የሚደረገው ሥራ እንደሚጠናከር አስታውቀዋል።