ያልተገባ የብሬስ ህክምና ለተወሳሰበ የጤና ችግር ሊያጋልጥ እንደሚችል ተጠቆመ‼️
የአፍና የጥርስ ጤናን በአግባቡ ለመጠበቅ የባለሙያዎችን ድጋፍ ማግኘት፣ እንደ ሲጋራ ማጨስና አልኮል መጠጣት ያሉ አደገኛ ልማዶችን ማስወገድ እንዲሁም ወቅታዊ የህክምና ክትትል ማድረግ ወሳኝ መሆኑን በጳውሎስ ሆስፒታል ጥርስና ማክሲሎፌሻል ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና የፊትና መንጋጋ ቀዶ ጥገና ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አዲስ ካሳሁን ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል። የአፍና የጥርስ ጤና ከውበት ገጽታ ባሻገር ከአጠቃላይ የጤና ሁኔታ፣ አደገኛ በሽታዎችን ከመከላከል እና ከስነ-ልቦናዊ ደህንነት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት እንዳለው ተገልጿል። የጥርስ ማስተካከያ ወይም የብሬስ ሕክምናዎችን በሚፈልጉበት ወቅት በዘርፉ በቂ ስልጠና እና ሙያዊ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች መታከም እንደሚገባ ተመላክቷል። የብሬስ ሕክምና የውበት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የጥርስ መነቀልን፣ የመሰበርን እና የስነ-ልቦና ጫናዎችን የሚከላከል በመሆኑ በባለሙያ ቁጥጥር ስር መከናወን ይኖርበታል ተብሏል። ሕክምናው በየጊዜው ክትትል ማድረግን የሚጠይቅ ነው የተባለ ሲሆን ጥንቃቄ ካልተደረገ በጥርስና በድድ ላይ የረጅም ጊዜ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተጠቁሟል። በሌላ በኩል በአፍ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ የካንሰር አይነቶች ከፍተኛ አደጋን የሚያስከትሉ መሆናቸውን ዶክተር አዲስ ገልፀዋል። የዚህ አደገኛ በሽታ ዋና ዋና መንስኤዎች እና አጋላጭ ምክኒያቶች ሲጋራ ማጨስ እና አልኮል መጠጣት መሆናቸው አስረድተዋል። በመሆኑም እነዚህን ጎጂ ልማዶች ማስወገድ እና የቅድመ መከላከል ምርመራዎችን ማድረግ የብዙዎችን ህይወት ለማትረፍ እንደሚረዳ ተነግሯል።