“በአስመራ አገዛዝና ደጋፊዎቹ ላይ በጊዜ እርምጃ አለመውሰድ ከባድ መዘዝ ያስከትላል”- ጌታቸው ረዳ
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ፣ ከአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድና የቀይ ባህር ቀጠና ልዩ መልዕክተኛ አኔት ወበር እና በኢትዮጵያ ከሚገኙት የህብረቱ አምባሳደር ሶፊ ጋር በቀጣናው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያዩ። በውይይታቸው በትግራይ፣ በኤርትራና በሱዳን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ጨምሮ ለቀጣናው ሰላምና ዘላቂ መረጋጋት ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ግልጽ የሃሳብ ልውውጥ ማድረጋቸውን ጌታቸው ረዳ ገልጸዋል። ጌታቸው ረዳ በተለይም በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ የሚገኘው አገዛዝና ደጋፊዎቹ በቀጣናው ውስጥ ያላቸውን አደገኛ ሚና በማንሳት፣ እንቅስቃሴያቸውን በጊዜ ለማስቆም አስፈላጊው እርምጃ ካልተወሰደ ከባድ መዘዝ ሊከተል እንደሚችል ለአውሮፓ ህብረት ተወካዮች ማስረዳታቸውን አስታውቀዋል። በመጨረሻም በቀጣናው ያለው ውጥረት እንዳይባባስ ለመከላከል፣ የመረጃ ልውውጥን ለማጠናከርና በቅንጅት ለመስራት መስማማታቸውን ጌታቸው ረዳ ገልጸዋል።