← All news
News Oct 13, 2026 · 25d ago

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የዳኝነት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል አሰራር መሸጋገሩ ተገለጸ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ሰሚ ችሎት የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ከዛሬ ጥቅምት 3 ቀን 2019 ዓ/ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል አሰራር መሸጋገሩን አስታውቋል። አሐዱ ሬዲዮ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ፣ ተደራሽ ፣ ግልጽ እና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ ያለመ "ሚዛንኢት" የተሰኘ የተቀናጀ የፍርድ ቤት ጉዳዮች መረጃ አስተዳደር ስርዓት ተዘርግቶ ወደ ስራ ገብቷል። የዚሁ ስርዓት የሙከራ ትግበራ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ተከትሎ በሰበር ሰሚ ችሎት ደረጃ የሚካሄዱ የዳኝነት አገልግሎቶች ከጅምር እስከ ፍጻሜያቸው ሙሉ በሙሉ በዚሁ ዲጂታል ስርዓት መከናወን መጀመራቸው ተገልጿል። በዚህም መሰረት በሰበር ሰሚ ችሎት አዲስ መዝገብ መክፈት የሚፈልጉ ተገልጋዮች ወደ ፍርድ ቤት በአካል መምጣት ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ሆነው በዲጂታል ስርዓቱ አማካኝነት መዝገባቸውን መክፈት እንደሚችሉ ተመላክቷል። በመታየት ላይ ባሉ ነባር መዝገቦች ላይ አገልግሎቱን ማግኘት የሚፈልጉ ተገልጋዮች መዝገቦቻቸውን ከፋይዳ ጋር ማስተሳሰር የሚኖርባቸው ሲሆን ይህንንም በመደበኛ የስራ ሰዓት በጠቅላይ ፍርድ ቤት በአካል በመገኘት ማከናወን ይችላሉ ተብሏል። አዲሱ "ሚዛንኢት" የተሰኘው ስርዓት ፍትህ የመጠየቅና የማግኘት ሂደቱን ዘመናዊ ፣ ፈጣን እና ለተገልጋዮች ምቹ የሚያደርግ እንደሆነ ተገልጿል።