← All news
News Oct 13, 2026 · 26d ago

ህፃናትን ጡጦ አስይዞ ማስተኛት ለጆሮ ኢንፌክሽን ሊያጋልጣቸዉ ይችላል ተባለ

👉 ይህ ድርጊት ህፃናቱን ለሳንባ ምች እና ለተደጋጋሚ ኢንፌክሽን የመጋለጥ ዕድላቸዉንም ሰፊ ያደርገዋል ነው የተባለው በግንዛቤ ማጣትም ይሁን በተለያዩ ምክኒያቶች ህፃናት እንዳያለቅሱ ተብሎ ጡጦ እየጠቡ እንዲተኙ ማድረግ ለተለያዩ የጤና ችግሮች ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸዉ ተጠቁሟል ። በሙራ የዉስጥ ደዌ እና ህፃናት ስፔሻሊስት ክሊኒክ ሜዲካል ዳይሬክተር እንዲሁም የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር አብዱልአዚዝ አሊ ለብስራት ሬዲዮ እንደተናገሩት ህፃናት ጡጦ ይዘዉ በሚተኙበት ወቅት ወተቱ በጥርሳቸዉ ዉስጥ በመከማቸት አሲድ ይፈጥርና ጥርሳቸዉ እንዲበሰብስ ምክኒያት ይሆናል ። ይህም የወደፊት ዋና ጥርሳቸዉን የአበቃቀል ሂደት ከማበላሸት ባለፈ የአነጋገራቸውን እና የፊት ቅርፃቸዉን ገፅታ ሊያበላሽ እንደሚችል ተመላክቷል ።የህክምና ባለሙያው አክለዉም ህፃናት ጡጦ ይዘዉ በሚተኙበት ሰዓት ለተደጋጋሚ የጆሮ ኢንፌክሽን የመጋለጥ ዕድላቸዉ ሰፊ ነዉ ያሉ ሲሆን ለህይወት አስጊ በሚሆን መልኩ ወደ መተንፈሻ አየር ቧንቧ በመሄድ መታነቅን ሊያስክትል ይችላል ብለዋል  ። ህፃናት ተኝተዉ ጡጦ መጥባታቸው ወተቱ ሳይታሰብ ወደ አየር መተላለፊያ ቱቦ እና ወደ ሳንባ ውስጥ ሊገባ ይችላል ። በዚህም የተነሳ ወተቱ በሳንባ ውስጥ በሚከማችበት ጊዜ ባክቴሪያዎች እንዲራቡና ከባድ የሆነ የሳንባ ምች እንዲከሰት ያደርጋል ተብሏል ።ህፃናት ለረጅም ሰዓታት ጡጦ ይዘዉ ሲተኙ በቀን ከሚያስፈልጋቸዉ ካሎሪ በላይ በመዉሰድ ላልተፈለገ ክብደትም እንደሚጋለጡ ዶክተር አብዱልአዚዝ ጨምረው ለጣቢያችን ገልፀዋል። ይህንን የጤና ችግር ለመከላከል ወላጆች ኃላፊነት መዉሰድ እንዳለባቸዉ አሳስበው ህፃናት ለሊት ጡጦ የሚጠቡ ከሆነ ጡጦ ይዘዉ እንዲተኙ ከማድረግ ይልቅ መጥባት ያለባቸዉን ያህል ከወሰዱ በኋላ ጡጦዉን ማንሳት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።