ወደ ኤርትራ መሸሽ ወደ ሲኦል እንደመሄድ ነው ሲል ቲፒኤፍ የሕወሓትን አመራሮች አስጠነቀቀ
የትግራይ ሰላም ኃይል (TPF) እንደገለጸው፣ የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር አካባቢ ተሰብስበው ይገኛሉ። የቡድኑ ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ፣ አመራሮቹ ወደ ኤርትራ መሻገር አለባቸው በሚሉና መሻገር የለባቸውም በሚሉ ወገኖች መካከል አለመግባባት መፈጠሩን ተናግረዋል። ቃል አቀባዩ የሕወሓት አመራሮች በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ላይ መሰብሰባቸውን እንደሚያውቁ ገልጸው፣ ወደ ኤርትራ መሸሽን ከከባድ አደጋ ጋር በማያያዝ አስጠንቅቀዋል። አመራሮቹና ታጣቂዎቹ አገራቸውን ጥለው ከመሄድ ይልቅ በኢትዮጵያ እንዲቆዩም ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪም የትግራይ መጻኢ ዕድል ብሩህ እንደሆነ በመግለጽ፣ ታጣቂዎችና ካድሬዎች ምሕረት እንደሚደረግላቸው ተረድተው ወደ አሃዶቻቸው በመሄድ እጃቸውን እንዲሰጡ መክረዋል።