← All news
News Oct 12, 2026 · 27d ago

ኤርትራ ሰራዊቷን ካላስወጣች ከእደጋ ሐሙሱ የበለጠ ጥቃት ይቀምሳል-አምባሳደር ጄኔራል ባጫ ደበሌ‼️

አምባሳደር ጄኔራል ባጫ ደበሌ የኤርትራ ኃይሎች የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው መግባታቸውን የሚያረጋግጥ በሳተላይት እና በቪዲዮ የተደገፈ ተጨባጭ ማስረጃ መኖሩን ይፋ አድርገዋል። ይህ ማረጋገጫ የተሰጠው፣ የኤርትራ መንግስት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተ.መ.ድ) የቀረበበትን የድንበር ጥሰት ክስ ሙሉ በሙሉ በመካድ "ኢትዮጵያ ለባህር በር ስትል ልትወረኝ ነው" የሚል የመልስ ክስ ማቅረቡን ተከትሎ ነው። ጄኔራሉ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መግለጫ፣ የአስመራ መንግስት እንደ ጥንቱ "ማንም አላየኝም" በሚል አስተሳሰብ ድንበር መጣሱን ቢያስተባብልም፣ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ግን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በሳተላይት እና በቪዲዮ መዝግቦ ይዟል ሲሉ የኤርትራን ክህደት ውድቅ አድርገውታል። በእነዚህ ተጨባጭ ማስረጃዎች መሰረት፣ የኤርትራ ወታደሮች ከዘመናዊ የድሮን ጥቃት ለማምለጥ ባህላዊ የቅጠል ሽፋን በመጠቀም በአርባ ገደማ ተሽከርካሪዎች አዲግራትን አልፈው ኢዳጋ ሐሙስ ድረስ ዘልቀው መግባታቸው ተረጋግጧል። ይሁን እንጂ ኃይሎቹ የተጠቀሙት ጊዜው ያለፈበት ስልት ከዘመናዊ የድሮን ጥቃት ሊያድናቸው ባለመቻሉ፣ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በገቡት ኃይሎች ላይ በመከላከያ ሰራዊቱ ጠንካራ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ጄኔራል ባጫ አብራርተዋል። "ቅጠላ ቅጠል አያድንህም"ም ብለዋል። በመጨረሻም ጄኔራሉ የማይካድ የቪዲዮ እና የሳተላይት ማስረጃ የቀረበበት ይህ የኤርትራ ኃይሎች ወረራ በአስቸኳይ ቆሞ ሰራዊቱ የኢትዮጵያን መሬት ለቆ ካልወጣ፣ ከኢዳጋ ሐሙሱ የከፋ ወታደራዊ እርምጃ እንደሚጠብቃቸው በማሳሰብ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል።