የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞችን የጫነች አውሮፕላን ዛሬ መቐለ አሉላ አባነጋ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መግባቷን ምንጮች ገለጹ።
የመቐለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ደስታ እምባዬ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት አውሮፕላኗ ዛሬ 7 ሰዓት አካባቢ በመቐለ ሰማይ ስታቋርጥ ሁለት ዓይነት ስሜቶች ተንጸባርቋል። አብዛኛው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን መሆኗን ያረጋገጠ ነዋሪ፤ የበረራው መጀመር አብሳሪ ድምጽ አድርጎ በማሰብ ደስታውን ሲገልጽ፤ በህጻናትና አንዳንድ እናቶች ደግሞ ድሮን መስሎአቸው የመደናገጥ ስሜት እንደፈጠረ እኒሁ የአይን እማኝ ገልጸውልናል። ዛሬ መቐለ የገባችው የኢትዮጵያ አየርመንገድ አውሮፕላን የአየር መንገዱ የቴክኒክና ሌሎች ሰራተኞችን የጫነች እንደሆነ ከምንጮቻችን ለመረዳት ችለናል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትላንት ዓርብ ባወጣው መግለጫ ተቋርጦ የነበረው የአዲስ አበባ/ መቐለ በረራ ነገ እሁድ እንደሚጀምር ማስታወቁ ይታወሳል። via.DW