የኢትዮጵያ አበዳሪ አገራት ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የ1 ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ያዥ ዓለማቀፍ ኢንቨስተሮች የቦንዱን አከፋፈል እንደገና ለማዋቀር ባለፈው ሰኔ ወር በመርህ ደረጃ የደረሱበትን ስምምነት አጸደቀ።
ኮሚቴው፣ ስምምነቱ 'ሁሉም አበዳሪዎች በእኩል መታየት አለባቸው' ከሚለው የቡድን 20 ማዕቀፍ መርህ ጋር የተጣጣመ መኾኑን ገልጧል። የአበዳሪ አገራት ኮሚቴ ስምምነቱን ማጽደቁ፣ ኢትዮጵያ ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ እንድትጀምር ያስችላታል። ኾኖም ስምምነቱ ቦንድ ያዦች ወደፊት በገበያ በሚወሠን ወለድ ከኢትዮጵያ የ1 ቢሊዮን ዶላር ቦንድ እንዲገዙ መፍቀዱ፣ ቦንድ ያዦች ከአበዳሪ አጋራት በተለየ እንዲጠቀሙ ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው ኮሚቴው ገልጧል።