የአዲስ አበባ ጉዳይ‼️
በአገራዊ ምክክር ጉባኤው 300 ያህል የኦሮሚያ ክልል ተመካካሪዎች፣ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ መኾኗን የሚያረጋግጥ ድንጋጌ በሕገመንግሥቱ ይካተት የሚለው ጥያቄያችን አማራጭ የሌለው ምክረ ሀሳብ ኾኖ ካልተያዘ ከጉባኤው እንወጣለን በማለት ማስጠንቀቃቸው ተሰምቷል። የአገራዊ ምክክር ኮሚሽንም፣ የጋራ ማረጋገጫ ቡድኑ ያመሳከራቸውን ምክረ ሀሳቦች ከማቅረቡ በፊት ስብሰባ ያልጠራውን የክልል ተወካዮች ጉባኤ ትናንት ሰብስቦ የኦሮሚያ ተመካካሪዎችን ቅሬታ አቅርቧል። የክልል ተወካዮች ጉባኤ፣ ቅሬታውን መርምሮ የመፍትሄ ሀሳብ የሚያቀርብ የ11 ክልሎች ፕሬዝዳንቶች፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ ሦስት የትግራይ ተወካዮች፣ አምስት የሃይማኖቶች ተወካዮች፣ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሁለት የወጣቶች ተወካዮች የተካተቱበት ኮሚቴ አቋቁሟል። ኾኖም በርካታ ተመካካሪዎች፣ የኦሮሚያ ተመካካሪዎች ቅሬታ ከምክክር ሂደቱ የወጣና ሂደቱን ወደ ኋላ የሚመልስ ነው የሚል ተቃውሞ አሠምተዋል ተብሏል። ለሥራ ቡድኖች ከቀረቡት 476 ምክረ ሀሳቦች ውጭ አዲስ የሚጨመር ወይም የሚቀነስ ምክረ ሀሳብ ካለ፣ ራሳቸውን ከጉባኤው ለማግለል የወሠኑ ተመካካሪዎች መኖራቸውም ታውቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ የምክክር ጉባኤው በእያንዳንዱ አጀንዳ ላይ የተጠናቀሩትን የመጨረሻ ምክረ ሀሳቦች በማዳመጥ ላይ መኾኑን ዛሬ ነሐሴ 15 ማምሻውን ገልጧል። የምክክር ጉባኤው የተጠራው፣ የኦሮሚያ ተወካዮችን ቅሬታ ይመረምራል የተባለው የክልል ተወካዮች ገባኤ ምን መፍትሄ አቅርቦ እንደኾነ ግን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ማወቅ አልተቻለም።