የሶላር ኃይል አቅርቦት ባላቸው አካባቢዎች ለአዲስ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ነፃ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ አገልግሎት ተጀመረ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከዋናው ግሪድ ርቀው በሶላር ኃይል ማመንጫዎች አገልግሎት በሚያገኙባቸው አካባቢዎች ላሉ አዲስ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ነፃ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ መግጠም መጀመሩን አስታውቋል። የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ አንዋር አብራር እንደገለጹት፤ አዲሱ አሠራር በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የገጠር ማኅበረሰቦች በኢኮኖሚ አቅማቸው ሳቢያ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዳይገለሉ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። አሠራሩ በሥራ ላይ ከዋለ በኋላም ባሉት ሁለት ሳምንታት ብቻ 3 ሺህ 364 ደንበኞች ነፃ ቆጣሪ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተቋሙ ገልጿል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እስካሁን ባከናወናቸው ሥራዎች 54 የሶላር ኃይል ማመንጫዎችን በመገንባት ከ11 ሺህ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አቶ አንዋር አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም ዜጎች እነዚህን መሠረተ ልማቶች በአግባቡ እንዲጠብቁና የፍጆታ ክፍያቸውን በወቅቱ እንዲከፍሉ ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል።