የቤት ኪራይ❗❗❗
በሐዋሳ የቤት ኪራይ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ነዋሪዎችን ለከፍተኛ ችግር መዳረጉ ተገለጸ ። በሐዋሳ ከተማ በቅርብ ጊዜ የታየው ያልተጠበቀ የቤት ኪራይ ዋጋ ንረት በነዋሪዎች ላይ የከፋ የኑሮ ጫና እና እንግልት እየፈጠረ ይገኛል። በርካታ አከራዮች ቀደም ሲል ይጠይቁት ከነበረው ዋጋ በእጥፍ እና ከዚያም በላይ በመጨመራቸው፣ በተለይም በወር ደመወዝ የሚተዳደሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፈተና ተዳርገዋል። ይህ የኪራይ ዋጋ ንረት ዋነኛ ምክንያት ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ ከቤት ንብረታቸው የተነሱ በርካታ ዜጎች በአንድ ጊዜ ወደ ኪራይ ገበያው መግባታቸው እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ አከራዮችም ይህንን የመኖሪያ ቤት እጥረት እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ዋጋውን እንዲሰቅሉት አድርጎታል። በዚህም ምክንያት ቤት ፈላጊዎች በተመጣጣኝ ዋጋ መኖሪያ ማግኘት ሲቸገሩ፣ ያገኙትም ቢሆኑ ከገቢያቸው ጋር የማይመጣጠን ከፍተኛ ክፍያ ለመክፈል ተገደዋል። ከዚሁ ከልማት ተነሾች ጋር ተያይዞ መንግሥት በተለይ ከመንግሥት ቤት ለሚነሱ ነዋሪዎች ቀድሞ ምትክና ማረፊያ አዘጋጅቶ ማንሳት ሲገባው፣ በቂ ዝግጅት ሳያደርግ ሰዎችን ከቤት በማስወጣቱ ለተጨማሪ እንግልት ዳርጓቸዋል። የሐዋሳ ከተማ የኮሪደር ልማት ከተጀመረ አሁኑ አንድ ዓመት ገደማ እየሆነው ቢሆንም፣ እስከ ዛሬ ድረስ ከቤታቸው ለተፈናቀሉት ነዋሪዎች ምትክ ቤት ተሠርቶ አልተረከበም። በተጨማሪም ምትክ ማቅረብ በማይቻልበት ሁኔታ ለቤት ኪራይ የሚከፈለው ክፍያ የወቅቱን የገበያ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ ነው ተብሏል። ለአነስተኛ ቤተሰብ በሐዋሳ የሚከፈለው የቤት ኪራይ ድጎማ በወር ከ4,000 እስከ 7,000 ብር ብቻ በመሆኑ ከወቅቱ የኪራይ ገበያ ጋር በፍጹም የማይመጣጠን ሲሆን፣ በአንፃሩ እንደ ይርጋለም ባሉ አቅራቢያ ከተሞች ለተነሾች ከ10,000 ብር በላይ ክፍያ እየተፈጸመ ማቆየት መቻሉ በሐዋሳ ያለውን ክፍተት አጉልቶ አሳይቷል። በመሆኑም ነዋሪዎቹ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደርና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በጉዳዩ ላይ በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገቡ ጠይቀዋል። ችግሩ የግል አከራይና ተከራይ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የኑሮ ውድነትን የሚያባብስ በመሆኑ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ተተግሮ እንደነበረው ሁሉ አከራይና ተከራይን በሕጋዊ ውል የሚያስተዳድርና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን የሚያስቀር ሕጋዊ የአሠራር ማዕቀፍ በሐዋሳም እንዲዘረጋ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።