← All news
News Aug 21, 2026 · 18d ago

ኤምባሲ በሌለባቸው ሀገራት ለሚኖሩ ዜጎች የፓስፖርት አገልግሎት የሚሰጥበት አዲስ አሠራር ተዘረጋ

በሊባኖስ: በሱዳን፣ በጆርዳንና  የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሌለባቸው ሀገራት የሚኖሩ ዜጎች ፓስፖርታቸውን ለማደስ የሚያስችላቸው አሠራር መዘርጋቱን ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር ቁይታ ያደረጉት የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አምቦ መቃሳ ገለጸዋል ። በእነዚህ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎች በአቅራቢያቸው በሚገኝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለምሳሌ በሱዳን ያሉ በደቡብ ሱዳን በኩል አገልግሎት እንዲያገኙ መመቻቸቱን አቶ አምቦ ገልጸዋል። በተጨማሪም ተቋሙ የባዮሜትሪክስ መረጃዎችን የሚቀዱ ተንቀሳቃሽ መሣሪያዎችን ወደ እነዚህ ሀገራት በመላክ ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው መረጃቸው እንዲያዝ ይደረጋል ብለዋል። ፓስፖርታቸው ለረጅም ጊዜ የተቃጠለባቸውና ወደ ሀገር ቤት መግባት የሚፈልጉ ዜጎች ደግሞ በ“ሊሴ ፓሴ”  የጉዞ ሰነድ ወደ ሀገራቸው ገብተው ፓስፖርታቸውን እንዲያድሱ መመሪያ መሰጠቱ ታውቋል። በተመሳሳይ በሀገር ውስጥ መጓዝ ለማይችሉ አረጋውያንና ሕሙማን በቤታቸው ተገኝቶ አገልግሎት የመስጠት መርሐ-ግብር በቅርቡ እንደሚጀመር ተጠቁሟል።