የቻይና ኩባንያዎች በ12.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በሚገነባው የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ላይ ለመሳተፍ ከቀረቡ ድርጅቶች ውስጥ የበላይነቱን ያዙ
በኢትዮጵያ በ12.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ በሚገነባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ላይ ለመሳተፍ ከቀረቡት ድርጅቶች ውስጥ አብዛኞቹ የቻይና ኩባንያዎች ወይም ከቻይና ኩባንያዎች ጋር የተመሰረቱ ድጅቶች መሆናቸውን የአቪዬሽን መረጃ አቅራቢ እና የዜና ፖርታል የሆነው ‘ch-aviation’ ዘግቧል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ ይፋ የተደረገው የእጩዎች ዝርዝር እንደሚያሳየው፣ የቻይና ኩባንያዎች በከፍተኛ ልዩነት ትልቁን ቁጥር የያዙ ሲሆን፣ ይህም በሀገሪቱ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክት ላይ የቻይና ኢንጂነሪንግ እና ግንባታ ድርጅቶች ያላቸውን የጎላ ሚና የሚያሳይ ነው። በተወዳዳሪነት የተመረጡት የቻይና ኩባንያዎች ቻይና ኮሙኒኬሽንስ ኮንስትራክሽን ካምፓኒ፣ ቻይና ኮንስትራክሽን ኤይትዝ ኢንጂነሪንግ ዲቪዥን፣ ቻይና ሮድ ኤንድ ብሪጅ ኮርፖሬሽን፣ ቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን፣ ቤጂንግ ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ግሩፕ፣ ቤጂንግ እርባን ኮንስትራክሽን ግሩፕ፣ ቻይና ፈርስት ሃይዌይ ኢንጂነሪንግ ካምፓኒ፣ ቻይና ናሽናል ኤሮ-ቴክኖሎጂ ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ ቻይና ሬይልዌይ ቤጂንግ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ፣ ሻንዶንግ ሉቂያኦ ግሩፕ ናቸው።