← All news
News Aug 19, 2026 · 20d ago

በአዲስ አበባ ከተማ ከ2 ሺህ በላይ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ህጋዊ እውቅና እንደተሰጣቸው ተገለጸ

በከተማዋ በባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ላይ በተደረገው ለውጥ ህጋዊ እውቅና እንዲኖራቸው መደረጉን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ለመናኸሪያ ሬድዮ አስታውቋል፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት በከተማዋ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ባጃጆች ሙሉ በሙሉ ህገ-ወጥ እና ሰሌዳቸው እውቅና ያልነበረው በመሆኑ ለወንጀልና ለፀጥታ ስጋት ተዳርገው እንደነበር የሚናገሩት የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ሽፈራው፣ ይህንን ችግር ለመፍታት በተዘረጋው አሰራር የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ ወጣቶች በህጋዊ መንገድ እንዲደራጁ መደረጉን እና 2 ሺህ 800 ባጃጆች በማህበር ተደራጅተው እውቅና ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ህጋዊ እውቅና ያገኙ ባጃጆች ከዋና ዋና መንገዶች ውጭ ባሉ እና የህዝብ ትራንስፖርት ባልደራሰባቸው አካባቢዎች ተሰማርተው በቀን እስከ 250 ሺህ ሰዎችን እያጓጓዙ እንደሚገኙ አቶ ዳኛቸው ገልጸዋል። ባጃጆቹ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር የስርቆትና ህገ-ወጥነት ስራዎችን በመከላከል ረገድ የሰላም አጋዥ ሃይል ሆነው በመስራት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። አዲስ አበባ የባጃጅ ከተማ ባለመሆኗ በሂደት እነዚህ አነስተኛ የትራንስፖርት አማራጮች በአውቶቡሶች፣ በትላልቅ ተሽከርካሪዎች እና በሜትር ታክሲዎች እየተተኩ እንደሚሄዱ አቶ ዳኛቸው ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት ዋና ዋና መንገዶችን ከመኖሪያ አካባቢዎች ጋር በማያያዝ ረገድ ባጃጆች ከፍተኛ ሚና በመጫወታቸው የተጀመረው ህጋዊ አሰራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። በተሻሻለው የባጃጅ አሰራር ህብረተሰቡ እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ አገልግሎት እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።