ትራምፕ ሆርሙዝ ሰርጥን ‘የአሜሪካ ግዛት ነው’ አሉ
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወሳኙን የሆርሙዝ የባህር ሰርጥ ‘አዲሱ የአሜሪካ ግዛት’ ነው ሲሉ አውጀዋል። ፕሬዚዳንቱ በትናንትናው እለት በትሩዝ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው በመካከለኛው ምስራቅ ባለው ውጥረት ሳቢያ በታሰበው ልክ አገልግሎት መስጠት ያልቻለውን የባህር መተላለፊያ ‘የአሜሪካ ግዛት’ ማለታቸው ተሰምቷል። ትራምፕ አሁን ላይ ከኢራን ጋር ምንም አይነት ድርድር እየተካሄደ አለመሆኑንና የተያዘ ቀነ ቀጠሮ አለመኖሩንም ገልጸዋል። የትራንስፖርት እንቅስቃሴውም ባለበት መሆኑን እና እስካሁን አገልግሎት አለመጀመሩን ገልጸዋል። ይህን ተከትሎ ኢራን የፕሬዚዳንቱን ንግግር “ቅዠት” በማለት፥ ቴህራን አሜሪካን “ታርማታለች” ስትል አስጠንቅቅለች። ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ካዘም ጋሪባባዲ ትራምፕ “የባህር ሰርጡን ትክክለኛ ስም አስተካክለው እንዲፅፉም” ጠይቀዋል። ጋሪባባዲ ይህን ያሉት ትራምፕ የባህር ሰርጡን ‘የአረብ ባህረ ሰላጤ’ በሚል መግለጻቸውን ተከትሎ መሆኑን አር ቲ አስነብቧል።