← All news
News Aug 18, 2026 · 21d ago

በጠለምት ወረዳ በተከሰተ ድርቅ የ16 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የመረው ቀበሌ አስተዳዳሪ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ

በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ መረው ቀበሌ በተከሰተው በረታች ድርቅ ሳቢያ የ16 ሰዎች ሕይወት ማለፉንና በመቶዎች የሚቆጠሩ የቤተሰብ አባላት ለስደት መዳረጋቸውን የመረው ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ ጥላሁን ገብረሚካኤል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ፣ በአካባቢው ከመጋቢት ወር ጀምሮ ምንም ዓይነት ዝናብ በመጥፋቱ አርሶ አደሩ የዘራው እህል ሳይበቅል ቀርቷል። በዚህም ምክንያት በአካባቢው የምግብ እጥረትና ረሃብ በመከሰቱ፣ የሰው ሕይወት ከማለፉ ባሻገር የቁም እንስሳትም በሙሉ ማለቃቸውን አክለዋል፡፡ በተጨማሪም ድርቁ ያስከተለው የረሃብን ሁኔታ መቋቋም የተሳናቸው 488 አባወራዎች ከአካባቢው ለቅቀው ወደ ምዕራብ ትግራይ መሰደዳቸውን ጥላሁን አስረድተዋል። ችግሩን በተመለከተ እስከ ክልል ድረስ አቤቱታ መቅረቡን የጠቆሙት አስተዳዳሪው፣ ከየቀበሌው የተመደቡ አካላት የሞቱ ሰዎችን፣ የተሰደዱ አባወራዎችን እና ያለቁ እንስሳትን ቁጥር መዝግበው ለሚመለከተው አካል ቢያሳውቁም እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ አለመገኘቱን ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም ከመንግሥት የተደረገው ድጋፍ ለአቅመ ደካሞች ብቻ የተሰጠ የሴፍቲኔት እርዳታ እንደነበርም አክለው ጠቁመዋል። እየከፋ የመጣውን የረሃብ አደጋ ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎች የድንገተኛ እርዳታ ጥያቄ በማንሳት ሰልፍ መውጣታቸውን የገለጹት ጥላሁን፤ አሁንም አስቸኳይ ድጋፍ ካልቀረበ የአካባቢው ሕዝብ በረሃብ የሚያልቅበት አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት በፍጥነት እንዲደርሱላቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።(አዲስ ማለዳ )