← All news
News Aug 18, 2026 · 21d ago

በኢትዮጵያ 4 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች በጡት ካንሰር ይጠቃሉ

የወንዶች የጡት ካንሰር የማይሰሩ የወተት ቱቦዎች፣ እጢዎች እና የጡት ቲሹዎች ላይ የሚከሰት የካንሰር አይነት መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ልክ እንደ ሴቶች ሁሉ የጡት ካንሰር በወንዶች ላይም በማንኛውም እድሜ ክልል ውስጥ ሊከሰት ይችላል ሲሉ በጳውሎስ ሆስፒታል የጡት ካንሰር ኢሜጂንግ ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ሜሮን አህመድ ከብስራት ሬዲዮ ጋር በነበራቸዉ  ቆይታ ተናግረዋል። በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር አይነቶች መካከል የጡት ካንሰር ቀዳሚውና በብዛት የሚታወቅ ቢሆንም በወንዶች ላይ የሚከሰተውን የጡት ካንሰር አስመልክቶ ግን በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑ ተጠቁሟል። በአለም አቀፍ ደረጃ በወንዶች ላይ የጡት ካንሰር የመከሰት እድሉ 1በመቶ እንደሚሆን ተገልጿል።  በኢትዮጵያ ደግሞ የመከሰት መጠኑ ከ3 እስከ 4 በመቶ እንደሚደርስ የሚያመላክቱ ሪፖርቶች መኖራቸውን ዶክተር ሜሮን ጠቅሰዋል። በሁለቱም ፆታዎች ላይ ካንሰር መኖሩ የሚታወቀው ጡት ላይ በሚፈጠር እብጠት ቢሆንም ማንኛውም የእብጠት ምልክት  ካንሰርን እንደማይጠቁም ዶክተር ሜሮን አሳስበዋል።እንዲሁም በተለምዶ የጡት ካንሰር የሴት ህመም ብቻ ተደርጎ መወሰዱ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመዋል። ስለሆነም ጡት ላይ የሚፈጠሩ እብጠቶች ህመም የላቸውም የሚሉ መዘናጋቶች የካንሰር ህመምን የሚያባብስ በመሆኑ እንዲህ ያሉ ምልክቶች ሲኖሩ የጡት ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ዶክተር ሜሮን ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።