← All news
News Aug 17, 2026 · 22d ago

በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ከ2 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 2 ሺህ 212 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።   በሳምንቱ ውስጥ በተደረጉ 10 ዙር የበረራ ጉዞዎች ወደ ሀገራቸው ከተመለሱት መካከል 2 ሺህ 210 ወንዶች፣ 1 ሴት እና 1 ጨቅላ ሕፃን የሚገኙበት ሲሆን፤ 38ቱ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ናቸው።   እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ፣ መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረውን ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ሥራ ተከትሎ እስካሁን ከ94 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው መመለስ ተችሏል።   ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለተመላሽ ዜጎች በአየር ማረፊያና በማቆያ ማዕከላት ተገቢውን ድጋፍና እንክብካቤ በማድረግ እንዲሁም ከቤተሰብ ጋር የመቀላቀል ሥራ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እያከናወነ ይገኛል።   በተጨማሪም መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ወደ ተለያዩ ሀገራት ሄደው የሚመለሱ የፍልሰት ተጎጂዎችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን፣ ወደፊትም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና ደህንነቱ የተጠበቀ ፍልሰትን ለማበረታታት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።