የኢሎን ማስክ አዲስ ህልም የጨረቃጉዞ ለሁሉም ሰው ክፍት ሊሆን ነው
ቢሊየነሩ ኢሎን ማስክ፣ ስፔስ ኤክስ የተሰኘው ኩባንያው የጨረቃ ጉዞን ለጠፈር ተመራማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ሰው ክፍት ለማድረግ ማቀዱን ተናገረ። ማስክ "ሙንቤዝ አልፋ" ብሎ በሰየማት የጨረቃ መንደር፣ መሄድ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው መጓዝ የሚችልበትን ትልቅ ህልም ይፋ አድርጓል። ኩባንያው ስታርሺፕ የተሰኘው መንኮራኩሩ በጠፈር ላይ ነዳጅ በመሙላት እስከ 100 ቶን የሚደርስ የመኖሪያ እና የግንባታ እቃዎችን ወደ ጨረቃ ማጓጓዝ ይችላል ብሏል። የአሜሪካው የጠፈር ተቋም (ናሳ) ሰዎችን ወደ ጨረቃ ለመመለስ ከስፔስ ኤክስ ጋር እየሰራ ቢሆንም፣ የዚህ ፕሮጀክት ዋና ፈተና መንኮራኩሩ በጠፈር ላይ እያለ ነዳጅ የመሙላቱ ሂደት እንደሆነ ተገልጻል። ናሳ ሂደቱ መዘገየቱን የጠቆመ ሲሆን፣ አንድን መንኮራኩር ወደ ጨረቃ ለመላክ ብቻ ከ11 በላይ የነዳጅ ጫኝ መንኮራኩሮች ጉዞ ሊያስፈልግ እንደሚችል ዘገባዎች አመልክተዋል።