በሱዳን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ 1.4 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ወደ ደቡብ ሱዳን መግባታቸው ተገለጸ
በደቡብ ሱዳን ለሚገኙ ስደተኞችም የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ ቀርቧል። ደቡብ ሱዳን በራሷ በኩል ከፍተኛ የሰብዓዊ እና የልማት ፈተናዎች ቢጋረጡባትም፣ ለስደተኞች ያላትን ክፍት ፖሊሲ አሁንም አጥብቃ መቀጠሏ ተገልጿል። ሆኖም የገንዘብ እጥረት የስደተኞችን የመቋቋም አቅም እየሸረሸረ መሆኑን የጠቆሙት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ (UNHCR) እና የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP)፤ ይህም የሲቪሎችን ሕይወት የበለጠ ለአደጋ እንደሚያጋልጥ አስጠንቅቀዋል። ተቋማቱ አክለውም የሕይወት አድን እርዳታ ስራዎች እንዳይቋረጡ እና በዚህ ቀጠናዊ ውጣ ውረድ ግንባር ቀደም ተጎጂ የሆኑ ቤተሰቦችን ለመደገፍ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ በጋራ ጥሪ አቅርበዋል።