← All news
News Aug 12, 2026 · 27d ago

የአሜሪካ ሴኔት ለ32 የአፍሪካ ሀገራት የሚሰጠውን የአጎዋ የንግድ ፕሮግራም ለማራዘም ወሰነ

የዩናይትድ ስቴትስ ሴኔት የአፍሪካ የእድገትና የዕድል ስምምነትን ለሁለት ዓመታት እንዲራዘም ያጸደቀ ሲሆን፤ ይህም ብቁ ከሆኑ ሀገራት የሚገቡ ከ1 ሺህ 8መቶ በላይ ምርቶች እስከ ታህሳስ 2028 ድረስ ከቀረጥ ነፃ ወደ አሜሪካ ገበያ እንዲገቡ ያስችላል። ለ25 ዓመታት የአሜሪካ-አፍሪካ የንግድ ግንኙነት መሰረት ሆኖ የቆየው አጎዋ፤ አሜሪካ 32 ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር የሚያወጡ መኪናዎችን፣ ልብሶችን እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ከቀረጥ ነፃ እንድትገዛ ዕድል ሰጥቷል። አሁን ያለው ስምምነት በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ሊያበቃ የነበረ በመሆኑ፤ ይህ ማራዘሚያ በአሜሪካ የኤክስፖርት ንግድ ላይ ለሚደገፉ የአፍሪካ የንግድ ተቋማት ትልቅ እፎይታ ሆኗል። ለማራዘሚያው መሳካት ድጋፍ ያደረጉት የአሜሪካው ሴናተር ራፋኤል ዋርኖክ፤‹‹ይህ ውሳኔ የዕለት ተዕለት ዕቃዎችን ዋጋ ከመቀነሱም በላይ፤ የዓለም አቀፍ አጋሮቻችንን ኢኮኖሚ በማረጋጋት የሀገራችንን ብሄራዊ ደህንነት ያሻሽላል›› ብለዋል።