← All news
News Aug 11, 2026 · 27d ago

ሶስት አሠልጣኞችና አራት አትሌቶች አሜሪካ ፖርትላንድ ላይ ኮበለሉ!

🔴 ቡድኑ በቺካጎ አድርጎ ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ 7 የቡድኑ አባላት ከልዑካን ቡድኑ ጋር የሉም 🔴 የአሜሪካኗ ዩጂን ኦሪገን ለኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ውጤት የሚመዘገብባት ከተማ ብቻ ሳትሆን በርካቶች የሚኮበልሉባት ታሪካዊ ከተማም ሆና ተመዝግባለች ✍️በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ(ሀትሪክ ስፖርት) በአሜሪካ ኦሪገን ዩጂን ሲካሄድ የነበረው ከ20 ዓመት በታች 21ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መጠናቀቁ ይታወሳል። ወደ ውድድሩ ስፍራ የተጓዘችው ሀገራችን ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው 2 ወርቅ፣3 ብር እና 1 ነሃስ በድምሩ 6 ሜዳሊያ ማግኘቷም ይታወቃል። ከወደ ኦሪገን ከደቂቃዎች በፊት የደረሠን አስደንጓጭ ዜና ለሻምፒዮናው ከተጓዙት የልዑኳን ቡድን አባላት መካከል ሰባቱ ፖሬትላንድ ላይ መኮብለላቸው ተረጋግጧል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የልዑካን ቡድን በአሁን ሠዓት ከፖርትላንድ ተነስቶ ወደ ቺካጎ አየር ማረፊያ እየተጓዘ ሲሆን እነዚሁ ሰባቱ የቡድኑ አባላት ከልዑኳን ቡድኑ ተለይተው መቅረታቸውን ነው ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል ያረጋገጠችው። እንደ ታማኝ የመረጃ ምንጮቻችን ከሆነ ከሄዱት አራት አሠልጣኞች ሶስቱ ከቡድኑ ጋር ባለመመለሳቸው በአሁን ሠዓት ወደ ኢትዮጵያ በመገስገስ ላይ በሚገኘው አውሮፕላን ውስጥ አንድ አሠልጣኝ ማለትም አሠልጣኝ መሠረት  ብቻ እንደሚገኝ ነው ምንጮቻችን የገለፁልን። አትሌቶቻችን በተመለከተ አራት አትሌቶች እንደኮበለሉ የገለፁልን የመረጃ ምንጮቻችን በወኪንግ፣በ800፣በ5ሺ እና በ3ሺ መሠናክል ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች ከቡድኑ ጋር አብረው እንዳልተመለሱና እንደኮበለሉ ነው የመረጃ ምንጮቻችን ጨምረው የገለፁልን። የአትሌቶቹና የአሠልጣኞቹ ሙሉ ስም የደረሳት ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል ለቤተሠቦቻቸውና ለደህንነታቸው ስትል የሁሉንም ስም ይፋ ከማድረግ ተቆጥባለች። የአሜሪካኗ ዩጂን ኦሪገን ለኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ውጤት የሚመዘገብባት ከተማ ቤቻ ሳትሆን በርካታ አትሌቶች፣አሠልጣኞችና  አመራሮች የሚኮበልሉባት ታሪካዊ ከተማ ሆና ተመዝግባለች።