የውጭ ሀገር ዜጋ በኢትዮጵያ የቤት ባለቤት ለመሆን ከ100 እስከ 150 ሺሕ ዶላር እንደሚያስፈልገው የሚደነግግ መመሪያ ወጣ።
መመሪያውን ያወጣው የኢትዮጵያ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ነው። ሐምሌ 2018 ዓ/ም መጨረሻ ላይ ጸድቋል። በመመሪያው መሠረት የውጭ አገር ዜጋ ማለት፤ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆነ የውጭ ዜጋን ሳይጨምር ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌለው ወይም የሌላ አገር ዜግነት ያለው ማንኛውም ሰው ማለት ነው። በዚህም መመሪያው ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተማ ላይ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን 150 ሺህ ዶላር እንደሚያስፈልገው ደንግጓል። በመመሪያው ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን ሊያሟላ የሚገባው ለአንድ መኖሪያ ቤት የሚያስፈልግ ዝቅተኛ የገንዘብ መጠን ተቀምጧል። ሸገር ከተማን ሳይጨምር በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በሶማሌ ክልል፣ በሐረሪ ክልል ወይም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን ደግሞ ዝቅተኛው የገንዘብ መጠን 120 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ማቅረብን ይጠይቃል። ከሌሎቹ ክልሎች የውጭ አገር ዜጋ የቤት ባለቤት ለመሆን ዝቅተኛ ገንዘብ የሚጠየቀው በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልል ሲሆን የገንዘቡ መጠን ደግሞ 100 ሺህ ዶላር እንደሆነ ተደንግጓል። አንድ የውጭ አገር ዜጋ በኢትዮጵያ ሊኖረው የሚችለው የቤት መጠን አንድ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ፈቃድ ወስዶ እያለማ ያለ ባለሀብት ግን ይህ ዝቅተኛ የገንዘብ መጠን ሳይገድበው የአንድ ቤት ባለቤት መሆን ይችላል።