በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 1,708 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ
በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ 1 ሺህ 708 ኢትዮጵያውያን በሳምንቱ ውስጥ በተደረገ ስምንት ዙር የበረራ ትራንስፖርት ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። ከተመለሱት ዜጎች መካከል 773 ወንዶች፣ 677 ሴቶች፣ 76 ጨቅላ ሕፃናት እና 163 ዕድሜያቸው ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ይገኙበታል። መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ከተጀመረው ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ዘመቻ ጀምሮ እስካሁን ከ92 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን በሰላም ወደ ሀገራቸው መመለስ ተችሏል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተመላሽ ዜጎች በአየር ማረፊያና በማቆያ ማዕከላት ተገቢውን ድጋፍና እንክብካቤ በማድረግ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማቀላቀል ሥራ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እያከናወነ ይገኛል። በተጨማሪም መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ተጎጂ የሆኑ ዜጎችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል። ወደፊትም በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አስከፊነት ዙሪያ ህብረተሰቡን የማስገንዘብ፣ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን የመከላከልና ደህንነቱ የተጠበቀ ሕጋዊ ፍልሰትን የማበረታታት ሥራዎች በትኩረት እንደሚሰሩ ተገልጿል።