የኤርትራ መንግስት ከህወሓት ታጣቂዎች ጋር በመቀናጀት ውጊያውን በኢትዮጵያ መሬት ላይ ለማድረግ በማቀድ፣ በሌሊት መብራት እያጠፋ ታንኮችን እና ከባድ መሳሪያዎችን ወደ ትግራይ ክልል እያስገባ መሆኑ ተጋለጠ።
ይህን ያልተጠበቀ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እና ጥምረት ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ራስን የመከላከል መብቱን ተጠቅሞ ኤርትራን ህጋዊ ኢላማ ሊያደርግ እንደሚችል በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ሱሌይማን ደደፎ በጥብቅ አስጠንቅቀዋል። በአሁኑ ወቅት የኤርትራ መንግስት ጦሩን በድብቅ ወደ ትግራይ ክልል እያስገባ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የኤርትራ ወታደራዊ አመራሮች በምስራቃዊ ዞን ዓዲግራት አካባቢ ከሚገኙ የህወሓት ወታደራዊ እና የሲቪል መስተዳድር አመራሮች ጋር ግንኙነት ሲያደርጉ የሚያሳዩ ምስሎች መውጣታቸው፣ የሁለቱን ኃይሎች አዲስ ጥምረት እያረጋገጠ ይገኛል። ይህንን የኤርትራን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አስመልክቶ በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ እጅግ ጠንካራ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። አምባሳደሩ እንዳብራሩት፣ አንድ የታጠቀ ወታደራዊ ኃይል የማዕከላዊ መንግስቱን ፈቃድ ሳያገኝ የአንዲትን ሉዓላዊት ሀገር ዓለም አቀፍ ድንበር አቋርጦ መግባት የተመሰረቱ የዓለም አቀፍ ህግ መርሆዎችን በግልጽ የሚጻረር ነው። ኤርትራ የታጠቀ ወታደራዊ ልዑኳን ወደ ትግራይ ክልል በመላክ እና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ከሚገኘው ቡድን ጋር በማገናኘት ይህንን ህግ ክፉኛ ጥሳለች። እንደ አምባሳደር ሱሌይማን ማብራሪያ፣ ይህ የኤርትራ እርምጃ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በከፍተኛ ሁኔታ የሚጥስ እና እጅግ የከፋ የቀጠናዊ ደህንነት መዘዝ የሚያስከትል ትንኮሳ ነው። ኤርትራ ይህንን እርምጃ መውሰዷ ቡድኑ በኢትዮጵያ ላይ ለከፈተው ጦርነት በቀጥታ አጋር እንደሆነች እና ጦርነቱን እንደተቀላቀለች ያስቆጥራል። በመሆኑም፣ የዚህ ዓይነቱ የሉዓላዊነት ጥሰት መፈጸም ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር እና በዓለም አቀፍ ህግ የተረጋገጠላትን ራስን የመከላከል (Self-defense) መብት ያለ አንዳች ገደብ እንድትጠቀም ያስገድዳታል። በዚህም መሰረት የሀገሪቱን ደህንነት ለማስጠበቅ ኢትዮጵያ ለምትወስደው ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ ኤርትራ ህጋዊ ኢላማ ትሆናለች። አምባሳደሩ በመጨረሻም፣ ኤርትራ ከዚህ ታጣቂ ቡድን ጋር የፈጠረችው ጥንቃቄ የጎደለው ጥምረት እና ህገ-ወጥ ድርጊት የራሷን የኤርትራን ሉዓላዊነት ጭምር ከባድ አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲሉ በማስጠንቀቅ መልዕክታቸውን አጠናቀዋል።