የመብራት ምሰሶዎችን ከገጩ አሽከርካሪዎች ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ የጉዳት ካሳ ተሰበሰበ
በአዲስ አበባ ከተማ በጥንቃቄ ጉድለት ምክንያት የመብራት ምሰሶዎችን ከገጩ አሽከርካሪዎች 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የጉዳት ካሳ መሰብሰቡን የአዲስ አበባ የመብራት አገልግሎት አስተዳደር ባለስልጣን አስታውቋል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሰብስብ ሁሴን እንደገለፁት ባለስልጣኑ ከተቋቋመ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የከተማዋን የመብራት አገልግሎት ዘመናዊ ለማድረግ የተለያዩ የልማትና የማሻሻያ ስራዎች ተከናውነዋል። በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት በከተማዋ የሚገኙ 41 ሺህ 283 የመብራት ምሰሶዎች በጂኦግራፊያዊ የመረጃ ሥርዓት እንዲመዘገቡ መደረጉ ተገልጿል። ይህ ሥርዓት የመብራት ምሰሶዎችን በዲጂታል መንገድ ለመከታተል፣ ቁጥጥርን ለማጠናከር እና የጥገና ሥራዎችን በፍጥነትና በብቃት ለማከናወን እንደሚያግዝ ተጠቁሟል። ባለስልጣኑ ለብስራት ሬዲዮ የላከው መረጃ እንደሚያመላክተው የከተማዋን የመብራት መሠረተ ልማት ይበልጥ ለማዘመን፣ የህዝብ ንብረትን ከጉዳት ለመጠበቅ እና ተመሳሳይ አደጋዎችን ለመቀነስ የቁጥጥርና የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው።