← All news
News Aug 5, 2026 · 33d ago

የኤቦላ ቫይረስ በአሳሳቢ ሁኔታ እየተሰራጨ ነው ሲል ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን አሳወቀ

የዛሬ ሁለት ወራት ተኩል ገደማ በኮንጎ የተከሰተው የኤቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ በአሳሳቢና ባልተጠበቀ ሁኔታ በሀገሪቱ እየተሰራጨ ነው ሲል ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በምህፃሩ MSF አስታወቀ። ድርጅቱ እንደሚለው በሽታውን ለመከላከል የህክምና ባለሞያዎች ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፤ ወረርሽኙ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሳሳቢ ሁኔታ እየተሰራጨ ይገኛል። እስካሁን ከ3 ሺህ 600 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በላቦራቶሪ ተረጋገጧል፤ ቁጥራቸው 1 ሺህ 500 የሚጠጋ ሰዎችም ሞተዋል። በአሁኑ ጊዜ ዋናው ተግዳሮት ባለሥልጣናት በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች መለየት እንደተሳናቸው መሆኑ ነው። ቡንያ በተባለው አካባቢ የሚገኝ የህክምና ማዕከል ውስጥ ከሚገኙት በሽተኞች ውስጥ 90 በመቶው ከዚህ ቀደም በኤቦላ ቫይረስ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ እንዳላቸው የሚታወቅ ነገር የለም። የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ኃላፊ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከመንግሥት ኃላፊዎችና ከሰብአዊ ድርጅቶች ጋር ለመነጋገር ዛሬ ወደ ኮንጎ ኪንሻሳ ሄደዋል። ዶክተር ቴዎድሮስ የኤቦላ ወረርሽኝ ከተሰከሰተ ወዲህ ወደ ኮንጎ ሲጓዙ የዛሬው ለሁለተኛ ጊዜ ነው።