← All news
News Aug 5, 2026 · 34d ago

የደረጃ ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮች እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በኦንላይን ክፍያ መፈጸም ይጠበቅባቸዋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ) ፦የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ መልዕክት የደረሳቸው የደረጃ ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮች እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በኦንላይን ክፍያቸውን በመፈጸም የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቀረበ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰውነት አየለ በሰጡት መግለጫ፣ቢሮው የግብር ስርዓቱን በማዘመን እና ፍትሃዊ አሰባሰብን በመዘርጋት ገቢን በጥራት እየሰበሰበ ይገኛል ብለዋል። ከተማ አስተዳደሩ ከሚሰበስበው ገቢ 72 በመቶውን ለዘላቂ ልማት፣ ለሰው ተኮር ፕሮጀክቶች እና ለኮሪደር ልማት በማዋል የመዲናዋን ገጽታና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እያጎለበተ ይገኛልም ብለዋል። በከተማዋ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ከ456 ሺህ በላይ የደረጃ «ለ» ግብር ከፋዮች አዲስ በተሻሻለው የገቢ ግብር አዋጅ መሰረት ግዴታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። ከደረጃ ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮች በዘንድሮ በጀት ዓመት 9.2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።