← All news
News Aug 5, 2026 · 34d ago

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ወደ መንግሥታዊ የልማት ድርጅት ተሸጋገረ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም (ፋይዳ) በይፋ"ፋይዳቨርስ" በመባል ወደ የመንግሥት የልማት ድርጅት ማዕቀፍ ማደጉ ተገለጸ። ይህ አዲስ ድርጅት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH) ሥር የተጠቃለለ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ ከነበረበት ማዕቀፍ ወጥቶ በንግድ አሠራር የሚመራ እና ዘላቂ ዲጂታል መሠረተ ልማት አቅራቢ ሆኖ እንዲቀጥል ታስቦ የተቋቋመ መሆኑ ተጠቁሟል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ እንደገለጹት፤ የዲጂታል መሠረተ ልማት ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለፋይናንስ አካታችነት እና ለቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ ወሳኝ ድርሻ አለው። ፕሮግራሙ አሁን ላይ ከ50 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን መመዝገብ የቻለ ሲሆን፣ 150 የሚደርሱ የንግድ ተቋማት የደንበኛ ማረጋገጫ (eKYC) ውህዶችን አከናውኗል። በተጨማሪም ከ190 ሚሊዮን በላይ ደህንነታቸው የተጠበቁ የማረጋገጫ ሂደቶችን በማከናወን ከ15 ሚሊዮን በላይ ዲጂታል መታወቂያ ምስክር ወረቀቶችን መስጠቱ ተገልጿል። ተቋሙ አሁን የያዘውን አዲስ መዋቅር በመጠቀም የዲጂታል መታወቂያ መፍትሔዎችን ከአህጉራዊ አጀንዳዎች ማለትም ከአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና  እና ከስማርት አፍሪካ ጋር ለማስተሳሰር እና አገልግሎቱን በክልሉ ለማስፋፋት ተነግሯል።