← All news
News Aug 4, 2026 · 35d ago

የ6ኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተናን 81 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ አላሳለፉም ተባለ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2018 ዓ.ም የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ማለፊያ ነጥብ ክልላዊ ፈተና 50 እና ከዚያ በላይ መሆኑን ገልጿል።ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ደግሞ 48 እና ከዛ በላይ ማለፊያ ነጥብ ተቆርጦለታል።የ8ኛ ክፍል ፈተናን ለመውሰድ የተመዘገቡ ተማሪዎች 86 ሺህ 502 እንደሆኑ የተገለፀ ሲሆን 78 ሺህ 203 የሚሆኑት ፈተናውን ወስደዋል።   ከእነዚህ ውስጥ ወደ ቀጣይ ክፍል ያለፋት 47 ሺህ 307 ተማሪዎች መሆናቸውን የጂንካ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የህዝብና ሚዲያ ግንኙነት  ዳይሬክተር አቶ የሱፍ አህመድ  ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።በዚህም መሠረት ክልላዊ ውጤት ከመቶ አንፃር ሲታይ 60 ነጥብ 4 መሆኑ ተገልጿል።በተመሳሳይ የ6ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ለመውሰድ የተመዘገቡ ተፈታኞች 126 ሺህ 224 ናቸው። ፈተና የወሰዱት ደግሞ 110 ሺህ 566  ከእነዚህ ደግሞ ማለፊያ ነጥብ አስመዝግበው ወደ ቀጣይ 7ኛ ክፍል የተዛወሩ 70 ሺህ 584 መሆናቸውን አቶ የሱፍ ነግረውናል።   በዚህም ክልላዊ ውጤት በመቶ ሲገለፅ 63 ነጥብ 8 እንደሆነ ተገልጿል። 540 ትምህርት ቤቶች የ8ኛ ክፍል ተማሪዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ አሳልፈዋል።በተመሳሳይ የ6ኛ ክፍል ፈተናን አስመልክቶ 476 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተማሪዎቻቸውን ሲያሳልፉ 81 ትምህርት ቤቶች ደግሞ አንድም ተማሪ አላሳለፉም።   በአጠቃላይ ክልላዊ ውጤቱ ከአምና የትምህርት ዘመን ውጤት ጋር ሲነፃፀር የ8ኛ ክፍል በ3 በመቶ ያነሰ አፈፃፀምን አስመዝግቧል ።  አምና በነበረው ክልላዊ ውጤት  63 በመቶ  የሆነ ውጤት ተመዝግቦበት እንደነበር ተገልጿል።በተመሳሳይ የ6ኛ ክፍል የአምና ክልላዊ ውጤትን በተመለከተ 56 በመቶ አፈፃፀም የታየበት እንደነበር የተነገረ ሲሆን በ2018 በጀት አመት ደግሞ 63 ነጥብ 84 በመቶ መሆኑን  አቶ የሱፍ አህመድ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።