በጻድቃኔ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ገዳም በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ የ14 ሰዎች ሕይወት አለፈ!
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኘው በጻድቃኔ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ገዳም ድንገት በተከሰተ የርዕደ መሬትና የመሬት መንሸራተት አደጋ የ14 ምዕመናን ሕይወት ማለፉንና በሰባት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን የዞኑ አስተዳደር መምሪያ አስታወቀ። በአደጋው በ5 ሰዎች ላይ ከፍተኛ እና በ2 ሰዎች ላይ ደግሞ መለስተኛ የአካል ጉዳት መድረሱን የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር መምሪያ ገልጿል። መምሪያው በአደጋው ህይወታቸውን ባጡ እና ጉዳት በደረሰባቸው ወገኖች የተሰማውን መሪር ኀዘን የገለጸ ሲሆን፣ አደጋው ከተከሰተ በኋላ በስፍራው በመገኘት የተቀናጀ የነፍስ አድኖና የሕክምና እርዳታ ድጋፍ ላደረጉት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ የማነብርሀን ተስፋ፣ የአመራር አካላት፣ ለፀጥታ ኃይሎች፣ ለሕክምና ባለሙያዎችና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ምስጋና አቅርቧል። በተጨማሪም በአደጋው ስፍራ በመገኘት ለሞቱት ጸሎተ ፍትሐት፣ ለተጎዱት ጸሎትና ለተከፉ ወገኖች የማጽናኛ ትምህርተ ወንጌልና አባታዊ ቃለ በረከት እየሰጡ ለሚገኙት ለብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቀሌምንጦስ ያለውን አክብሮት ገልጻል።