የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰራተኞቹን የቤት ችግር ለመፍታት በጀመረው ስራ በጥር ወር 2 ሺ 500 የሚሆኑ ቤቶች ግንባታ ይጠናቀቃል አለ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ 9 አዳዲስ የጉዞ አውሮፕላኖች እና ስምንት ዲኤ 40 ኤንጂ የተሰኙ ለፓይለቶች ማሰልጠኛ የሚሆኑ 8 አውሮፕላኖች መገዛታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተርሚናሎችን የማደስና እንደ አዲስ የመስራት ተግባራት ተከናውነዋል ነው ያሉት፡፡የሰራተኞችን የቤት ችግር ለማቃለል በተጀመረው ስራ 5 ሺህ ለሚሆኑ ሰራተኞች የቤት ግንባታ መጀመሩን ጠቁመው፤ 2 ሺህ 500 የሚሆኑት ቤቶች እስከ 2019 ዓ.ም ጥር ወር ድረስ እንደሚጠናቀቁ አብራርተዋል፡፡ ቀሪዎቹ ቤቶች ደግሞ በ2019 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃሉ ነው ያሉት፡፡የአየር መንገዱ የአቪየሽን ዩኒቨርሲቲ ከተቀበላቸው 2 ሺህ 183 ተማሪዎች ውስጥ 1 ሺህ 713 ተማሪዎችን ማስመረቅ መቻሉን አስረድተዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ አየር መንገዱ ለበጎ አድራጎት ስራዎች ከ5 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡