በኢትዮጵያ በመጪዎቹ ዓመታት ሥራ አጥነት ፈታኝ እንደሚሆን የዓለም የሥራ ድርጅት ገለጸ
የዜጎች ማኅበራዊ ጥበቃ አገልግሎት እንዲጨምር ጠይቋል በትምህርት ያልገፉና የሥራ ልምድ የሌላቸው ወጣቶች በክህሎት ማነስና በራሳቸው ሥራ ለመጀመር በሚገጥማቸው የፋይናንስ ችግር የሥራ ዕድል ዕጦት እንደሚያጋጥማቸው፣ የዓለም የሥራ ድርጅት (ILO) ገለጸ፡፡ የዓለም የሥራ ድርጅት ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከዩናይትድ ኪንግደም ተራድኦ ድርጅት (ዩኤአይድ) እና ከሌሎች ተቋማት በጋራ በመሆን፣ በማኅበራዊ ጥበቃ ላይ ያዘጋጀውን ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ ነው ይህንን የገለጸው፡፡በሪፖርቱ መሠረት ቁጥራቸው እያደገ ያለው ሥራ ፈላጊ ወጣቶች፣ በክህሎት ክፍተትና የራስን ቢዝነስ ለመጀመር በሚገጥማቸው የፋይናንስ ዕጦት ከፍተኛ ተግዳሮት ይገጥማቸዋል፡፡ የሕፃናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ወደ ሥራ ሊገባ የሚገባውን የወጣት ቁጥር የሚያሳድገው በመሆኑ፣ ዕድገቱን ከከተሞች የሥራ ገበያ ዕድል ጋር አጣጥሞና አዋህዶ መሄድ ከፍተኛ ፈተና ይሆናል ብሏል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር 17.6 በመቶ እንደሚደርስ ጠቅሶ፣ አካታችና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ተሳትፎን የሚደግፉ ፖሊሲዎችና መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ገልጿል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሥራ ብቁ የሆነው የሕዝብ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2015 ከነበረበት 54.7 ሚሊዮን እ.ኤ.አ. በ2025 74.8 ሚሊዮን፣ እ.ኤ.አ. በ2030 ወደ 85.3 እንደሚደርስ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡